ምስስል
ምስስል በየሳይንስ ፍልስፍና ውስጥ የአንድ አመክንዮአዊ ዓረፍተ ነገርን እውነትነት እና ውሸትነት መካከል ያለውን ልዩነት መለያ ዘዴ ነው። መነሻው ሃሳብም ማናቸው የሳይንስ ኅልዮቶች በአጠቃላይ መልኩ ውሸት ቢሆኑም ፣ ዳሩ ግን አንዳቸው ከሌላው በተሻለ መልኩ ወደ እውነቱ ይቀርባሉ። ስለዚህ ምስስል አንድ የሳይንስ ኅልዮት ለእውነቱ ወይንም ለሃቅ ከሌሎች ኅልዮቶች በተሻለ ቀርቦ እንደሚገኝ የሚታዎቅበት ዘዴ ነው።
እንደ ፈላስፋው ካርል ፓፐር፣ አንድ ኅልዮት ከሌላው ኅልዮት ወደ እውነቱ የበለጠ የቀረበ እንደሆነ እሚወስነው ነገር ያ ኅልዮት ያለው እውነት እና በውስጡ ያዘለው የእውነት መጠን ናቸው። አንድ ኅልዮት ከሌሎች ኅልዮቶች ጋር ሲዎዳደር የበዛ እውነታ በውስጡ ካዘለ፣ ወደ እውነቱ ይቃረባል፣ ሃቅን ይመሳሰላል እንላለን።
የኢሳቅ ኒውተን የእንቅስቃሴ ህግጋት ከፈላስፋው አሪስጣጣሊስ ይበለጠ እውነቶችን ያዘለ ነበር። ሆኖም የሁለቱም ኅልዮቶች በውስጣቸው ውሸት እንዳለባቸው የታዎቀ ነው። ይሁን እንጂ የኒውተን ኅግጋት ለእውነቱ የበለጠ ይቀረበ ነበር። በሌላ ጎን ሁለት ኅልዮቶች ወይንም አረፍተ ነገሮች እኩል እውነት ቢሆኑም ቅሉ በውስጣቸው ያዘሉት የእውነት መጠን አንዱን ከሌላው ይበለጠ ምስስል እንዲኖረው ያደርጋል። ለምሳሌ "በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ዝናብ ይዘንባል" የሚለው አባባል እውነት ቢሆንና ሌላ ዓረፍተ ነገር «በሚቀጥለው ሳምንት ሊዘንብ ወይንም ጸሐይ ሊዎጣ ይችላል» ቢል፣ ምንም እንኳ ሁለቱም ዓረፍተ ነገሮች እውነት ቢሆኑም የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ከሁለተኛው አረፍተ ነገር በበለጠ ለእውነቱ ይጠጋል፣ ስለሆነም የበለጠ ምስስል አለው እንላለን።